ለእያንዳንዳቸው አባላቶቻችን ደረጃውን የጠበቀ የላቀ ጥራት ያለው የአክሲዮን (የዕጣ) ሰርተፊኬት ተዘጋጅቶ ተጠናቋል። ይህ ዝግጅት ሰነድ ከመስጠት ባለፈ ለማህበረሰባችን ትልቅ እና ልዩ ትርጉም ያለው ተግባር ነው።
ከሰነድ አልባነት ወደ ህጋዊ ባለቤትነት
በማህበረሰባችን ውስጥ ብዙዎች በልፋትና በላባቸው ንብረት አፍርተው፣ ነገር ግን ሀብታቸው ህጋዊ ማረጋገጫ (ሰነድ) ስለሌለው ብቻ ሲፈርስባቸውና መብታቸውን ሲያጡ በተደጋጋሚ አይተናል። በተለይም፦
- በአሁኗ ሸገር ሲቲ (በአዲስ አበባ ዙሪያ) የሚኖሩ ሸማኔዎች ያፈሩት ሀብት፣
- በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ንብረት፣
እነዚህ ሀብቶች “ሰነድ አልባ” በመሆናቸው ብቻ፣ ባለቤቶቹ የባለቤትነት መብታቸውን መከላከል እንዳይችሉ ከማድረጉም በላይ፣ ለደረሰባቸው ጉዳት ተመጣጣኝ ምትክ ወይም ካሳ ለመጠየቅ የሚያስችል መነሻ በማጣታቸው ለከፍተኛ እንግልት ሲዳረጉ ቆይተዋል። አብዛኛው የማህበረሰባችን ክፍል ዋስትና ሊሆን የሚችልና በህጋዊ ሰነድ የተደገፈ ሀብት የመያዝ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።
ዘላቂ መፍትሄ ለተሳታፊዎቻችን
ስለዚህ ይህንን የአክሲዮን ሰርተፊኬት ለአባላት ስናስረክብ፣ የአክሲዮን ድርሻ ማረጋገጫ ከመስጠት ባለፈ፣ የማህበረሰባችንን ስር የሰደደ የሰነድ አልባነት ችግር በዘላቂነት እየፈታን መሆኑን እንረዳለን። ይህ ሰነድ አባላቶቻችን በህግ ፊት የሚታወቅ፣ እንደ ዋስትና ሊያገለግል የሚችልና የባለቤትነት መብታቸውን የሚያስከብር እውነተኛ ሀብት በእጃቸው እንዲገባ ያደርጋል።
ትጉህ እጅ ትገዛለች!